ዐምደ ጽዮን

(ከአምደ ጽዮን የተዛወረ)

ቀዳማዊ ዐጼ ዐምደ፡ጽዮን (የዙፋን ስም ገብረ መስቀል) ከ1314 እስከ 1344 ዓ.ም. የነገሡ ሲኾን በጥንቱ ዘመን ከተነሱ ነገሥታት ውስጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሰፋ ያለ አሻራ ትተው ካለፉት (ለምሳሌ፦ ዘርዐ ያዕቆብ ) ጎን ወይም በላይ ስማቸው ይጠቀሳል[1] ። ዐጼ ዐምደ ጽዮን የዐጼ ይኩኖ አምላክ የልጅ ልጅና የዐጼ ወድም አራድ ልጅ እንደሆኑ ይታመናል[2]፡፡ ይኩኖ አምላክ አዲሱን የሰሎሞን ሥርወ መንግሥት ቢመሰርቱም፣ በልጅ ልጆቻቸው የነበረው ፉክክርና አዲስ ከሚስፋፋው የእስልምና ሃይማኖት የሚሰነዘረው ጥቃት ስርዓቱን ስጋት ላይ የጣለ ነበር። ዐጼ ዐምደ ጽዮን ይህን ፉክክር በማስቆምና በዘመናት በማይደበዝዘው ጀግንነታቸው የኢትዮጵያን ድንበር ከሞላ ጎደል አሁን በሚታወቀው መልኩ በማስቀመጥ፣ የዐዲሱን ሥርወ መንግሥት መሰረት በማጽናት እንዲሁም በማረጋጋት ዝናቸው በጥንቱ አለም ክአፍሪቃ ቀንድ እስከ አውሮጳ የተንሰራፋ ነበር [3]

ዐፄ ዐምደ ጽዮን
የዐጼ ዐምደ ጽዮን ደብዳቤ በቫቲካን ቤተ መጻህፍት ለ700 አመታት የተቀመጠ
የዐጼ ዐምደ ጽዮን ደብዳቤ በቫቲካን ቤተ መጻህፍት ለ700 አመታት የተቀመጠ
ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ግዛትከ1314-1344
ቀዳሚዐፄ ወደም አራድ
ተከታይዐፄ ነዋየ ክርስቶስ
ባለቤትብሌን ሳባ
ሙሉ ስምገብረ መስቀል
ሥርወ-መንግሥትሰሎሞን
አባትወደም አራድ
ሀይማኖትየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና


የአጼ ዐምደ ጽዮን ዘመንና ዘመቻዎች

ዘመቻ ወደ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ኢትዮጵያ

ዐምደ ጽዮን በእንዴት መንገድ ወደ ስልጣን እንደመጡ መረጃ የለም፣ ስለሆነም ታሪክ አጥኝው ታደሰ ታምራት ንጉሱ ከአባታቸው ጋር ትግል ገጥመው ዘውድ ላይ እንደወጡ መላ ምት ያቀርባል [4] ። ንጉሱ በመንግስታቸው መጀመሪያ (፲፫፻፲፮ ዓ.ም. ) የተሳካላቸው ዘመቻዎች በጎጃም፣ ዳሞትና ሐድያ በማድረግ እኒህ አካባቢወች እንዲገብሩ ሆነ[5]። ሆኖም በኒህ ዘመቻወች ትኩረታቸው ስለተሳበ በተገኘው ክፍተት የእንደርታ ገዢ የነበረው ይብቃ እግዚ የአምባ ሰናይት፣ ብልሃትንና ተምቤን ሰራዊትን በማደራጀት በንጉሱ ላይ ተነሳ [6]። በ1320ዓ.ም ንጉሱ የይብቃ እግዚን አመጽ ከደመሰሱ በኋላ በአምባ ሰናይት የጦር ዕዝ አቋቋመው ወደ ስሜን በመዝመት እስከ ቀይ ባህር ድረስ ያለውን ክፍል ለመቆጣጠር ቻሉ [7]። በዚህ ወቅት እንደረታን እንድታስተዳድር የተሰየመችው የትግሬ ተወላጅ የነበረችው የንጉሡ ሚስት ንግሥት ብሌን ሳባ ነበረች። ስልጣኗም ባልታ ብሃት በመባል ይታወቅ ነበር። ቆይቶ እንደርታን እንዲያስተዳድር የተደረገው የንጉሱ ሦሥተኛ ልጅ ባህር አሰገድ በማዕከለ ባህር ማረግ ነበር፣ ግዛቱም እስከ ቀይ ባህር ወደብ ድረስ የተንሰራፋ ነበር [8]

ዘመቻ ወደ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ

የንጉሱ ትኩረት ወደ ሰሜን መሆኑን የተረዱት የደቡብ እስላማዊ ክፍሎች፣ በቀይ ባህር ንግድ ላይ ያላቸውን ቁጥጥር እና ሃይል ተመርኩዘው የአርብቶ አደሩን ክፍል በማስተባበር የሃይል ማደግ አሳዩ። በተለይ በወላስማ ሱልጣኖች የሚመራውና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኘው የይፋት ግዛት በሃይል ተጠናከረ። ይህ ክፍል፣ ከአጼ ዐምደ ጽዮን ዘመን በፊት ጀምሮ ለመካከለኛው የኢትዮጵያ መንግስት ግብር ከፋይ ነበር። ሆኖም ክፍሉ በዚህ ዘመን እራሱን ችሎ ለመገንጠል ፈለገ [9]። በዚህ ሁኔታ የክርስቲያንና የእስልምና ግዛት በሰሜንና በደቡብ እየተጠናከሩ ሁለት የሃይል ማዕከሎች በመፍጠር ፉክክር ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ጦርነት መነሳቱ ግድ ሆነ።

ወደ ግብጽ ተልኮ የነበረው ጥንታይ የተሰኘው የንጉሡ መልዕክተኛ ሃቀዲን በተባለ የይፋት ገዢ መታሰር በመጨረሻ ጦርነቱ ገንፍሎ እንዲወጣ አደረገ። ዐምደ ጽዮን ይፋትን ከደመሰሰ በኋል በጀበልና ወርጂ አርብቶ አደሮች ተቃጥቶበት የነበረውን ጥቃት ድል በማድረግ እንዲሁም የክርስቲያን ክፍሎች፣ ተጉለት፣ ዝጋ ና መንዝ አመጾችን በማጥፋት ሃቃዲንን በማሰር ከስልጣን አስወገደው ። በርሱ ቦታ ወንድሙን ሰአደ'አድዲን አህመድን ከላይ የተገለጹት ክፍሎችን አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመው።




ስምንቱ የደቡብ መንግስታትም፣ የሱማሌንና የሃድያን ጨምሮ ለሱ ግብር ይከፍሉ እንደነበር ሳልት የተሰኘው የእንግሊዝ ጻህፊ ዘግቦት ይገኛል። የኢትዮጵያም ድበር በኢየሩሳሌም የተከፈተው በኒሁ ንጉስ መልካም ፈቃድ ነበር። ከዚህ በተረፈ «የወታደሩ እንጉርጉሮ» የተሰኙት አራቱ የአማርኛ መዛግብት በዚህ ዘመን እንደተጻፉ ታሪክ ዘጋቢወች ይናገራሉ።


ማጣቀሻ