ጎርፍ

ጎርፍ ወይም የውሃ መጥለቅለቅ ማለት በተለምዶ ደረቅ የሆነ መሬት በውሃ መሞላት ነው። ጎርፍ ብዙ ጊዜ በመኖሪያና የንግድ ተቋማት ላይ ጉዳት ያደርሳል። ሆኖም በወንዞች አካባቢ ያለው መሬት ጠፍጣፋ እና ለም ስለሆነ ሰዎች በውሃ ዳርቻ ይሠፍራሉ። አንዳንድ ጉርፎች ቀስ ብለው የሚያጥለቀልቁ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ በጥቂት ደቂቃዎች በፍጥነት ይሞላሉ።

በዝናብ እና ትልቅ ማዕበል የተከሰተ ጎርፍ በዳርዊን፣ ሰሜናዊ ግዛት፣ አውስትራልያ
ንጉሥ አብዱላ ጎዳና ተጥለቅልቆ በጅዳ፣ ሳዑዲ አረቢያ
በኸሪኬን ዊልማ በኦክቶበር 2005 እ.ኤ.አ. የተከሰተ ጎርፍ ኪይ ዌስት፣ ፍሎሪዳአሜሪካ አካባቢ
ጎርፍ በናታል፣ ሪዮ ግራንድ ዶ ኖርቴ፣ ብራዚል ውስጥ (ኤፕሪል 2013 እ.ኤ.አ.
በከባድ ዝናብ የተከሰተ ፈጣን ጎርፍ በቱዉምባ፣ ክዊንስላንድ፣ አውስትራልያ

ዋና የጎርፍ ዓይነቶች እና መንስዔዎቻቸው

ከዝናብ ጋር የተያያዘ

በጠፍጣፋ ወይም ዝቅ ባለ ቦታ ላይ የዝናብ ውሃ ወደ መሬት ቶሎ መዝለቅ ካልቻለ ወይም በአስፋልት ወይም ሌላ ደረቅ ንጣፍ ከተከለከለ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል።

የወንዝ ሙላት

ተከታታይ ዝናብ ወይም ፈጣን የበረዶ መቅለጥ ወንዝ እንዲሞላና እንዲያጥለቀልቅ ያደርጋል። ይህም ክስተት በመሬት መንሸራተት፣ ቆሻሻ ወይም ሌላ እንቅፋት ሊባባስ ይችላል።

የባህር ዳርቻ

በባህር ዳርቻ እና በወንዝና ባህር መገናኛ /estuary/ ቦታ ላይ በነፋስ እና ዝቅ ያለ የአየር ግፊት የሚከሰት የውሃ ማዕበል ጎርፍን ሊያስከትል ይችላል። በአውሎ ነፋስ ወይም ሱናሚ /tsunami/ የሚነሳ መጥለቅለቅም በዚህ ክፍል ውስጥ ይመደባል።

ድንገተኛ አደጋ

እንደ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም እሳተ ገሞራ ያሉ ድንገተኛ አደጋዎች ጉርፍ ሊያስነሱ ይችላሉ። በተጨማሪም በግድብ መፍረስ ወይም ሌላ የመሰረተ ልማት መበላሸት የሚከሰት ጎርፍ በዚህ ምድብ ውስጥ ይጠቃለላል።

ጉዳት

ወዲያው የሚከሰት ጉዳት

የጎርፍ ዋና ጉዳቶች የሰውና እንስሳ ሞት፣ የሕንጻዎች መፍረስ እና የመንገድ፣ ድልድይና ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ መበላሸት ናቸው።

የመሠረተ ልማት መውደም የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ እና ማመንጫዎችን ከሥራ ውጭ ሊያደርግ ይችላል። የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ደግሞ በርካታ ሂደቶችን ያስተጓጉላል። ለምሳሌ የውሃ ማጣሪያ እና ማቅረቢያ ተቋማት አገልግሎት ሊያቆሙ ይችላሉ።

የንፁህ ውሃ እጥረትና የፍሳሽ ውሃ ከጎርፍ ጋር መቀላቀል እንደ ታይፎይድ እና ኮሌራ ዓይነት የውሃ ወለድ በሽታዎች መንስዔ ሊሆን ይችላል።

በመንገድ እና ሌላው መሠረተ ልማት ላይ የደረሰ ጉዳት የጎርፍ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ወይም በአስቸኳይ ለማከም በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት ይሆናል።

በጎርፍ የተጥለቀለቀ የእርሻ መሬት ላይ እህል መዝራት ወይም መሰብሰብ ስለማይቻል ከጥቅም ውጪ ይሆናል። ይሄም ለምግብ እጥረት ይዳርጋል። ጎርፉ እጅግ በጣም ከፍተኛ ከሆነ የአንድ አገር እህል በሙሉ ሊጠፋ ይችላል። አንዳንድ የዛፍ ዝርያዎች ለረዥም ጊዜ ስራቸው በውሃ ከተጥለቀለቀ በሕይወት ላይቆዩ ይችላሉ።[1]

የረጅም ጊዜ ጉዳት

የቱሪዝም መዳከም፣ የመጠገኛ ወጪ እና የቁሳ ቁስ ዋጋ ንረት በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርገው ተጽዕኖ በአብዛኛው ጊዜ ከከፍተኛ መጥለቅለቅ በኋላ ይታያል። የሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም የሥነ ልቦና ችግር ሊፈጥር ይችላል።

የጎርፍ ትንበያ

ጉርፍ ከመድረሱ በፊት መተንበይ ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲወሰዱ እና የሚመለከተው ህብረተሰብ እንዲጠነቀቅ ጊዜ ያሰጣል።

ትክክለኛ ትንበያ ለመስጠት የአንድ ወንዝን ፍሰት ከዝናብ መጠን ጋር የሚያገናኝ ታሪካዊ መረጃ ወይም ሬከርድ ያስፈልጋል። ይህን ታሪካዊ መረጃ ከጊዜው የአየር ትንበያ እና የአካባቢው መሬት ሁኔታ ጋር በመቀላቀል የጎርፉን መድረሻ ጊዜ እና ከፍታ አስቀድሞ መገመት ይቻላል።

ማመዛገቢያ

የውጭ መያያዣ